የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአንድ ዓመት በላይ ሲያስተባብር የነበረው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በተመረጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲደረግ የነበረው ውይይት ተጠናቀቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአንድ ዓመት በላይ ሲያስተባብር የነበረው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በተመረጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረግ ውይይት መጠናቀቁን ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም. አሳወቀ። አምስቱም የቦርዱ አመራር አባላት፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረ-ሥላሴ፣ የውይይቱ ተሣታፊ የነበሩ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ታዛቢዎች፣ የውይይቱ መነሻ ሃሳብ የሚሆን ጥናት ያቀረቡ ባለሞያዎች እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን የተገኙበትን የውይይቱን መጠናቀቅ ማብሰሪያ መርኅ-ግብር በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም በታኅሣሥ 2011 ዓ.ም. የተጀመረውን ፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመረጡ ወሣኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የማወያየቱ ሃሳብና አጠቃላይ ሂደት አድካሚና በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈ እንደመሆኑ በመጠናቀቁ ተሣታፊ የሆኑትን ሁሉ የሚያኮራ እንደሆነና ዐላማውም ፓርቲዎች የሚወያዩበትን መድረክ መፍጠርና በሂደቱም የዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማጎልበት እንደነበር አስታውሰው ተሣታፊ የነበሩትን በሙሉ አመስግነዋል።
በመድረኩ ላይ የውይይቱን መጠናቀቅ ከማብሰር ባሻገር፤ በውይይቱ ላይ የተሣተፉትን በሙሉ ዕውቅና መስጠትና የውይይቱን ቃለ-ጉባዔ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማስተላለፍ ኮሚሽኑ ለሚሠራው ሥራ በግብዓትነት እንዲጠቀመው ሲል ቦርዱ ሠነዱን ለኮሚሽኑ አስረክቧል።
የመድረኩን የመዝጊያ ንግግር የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም የተጠናቀቀው በፖለቲካ ፓርቲዎቸ መካከል ሲደረግ የነበረው ውይይት፤ ለሀገር ግንባታ ሂደቱና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት እንዲሁም በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገት ላይ በጋራ ለመሥራት ለሚያስፈልገው ትብብርና ተግባቦት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነና ዐቅማችንንም ጭምር ያሳየንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል። የተደረጉት ውይይቶች ተሣታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከቆሙለት ዐላማና ዕምነት ባሻገር የሌሎችን ሃሳብ ለመስማትና ለማስተናገድ ዝግጁ ሆነው የቀረቡበትና የራሳቸውንም ሃሳብ እንዲሁ በነፃነት ያጋሩበት እንደነበር አስታውሰው፤ ይኽውም እኛን የሚመጥነንና ለተተኪው ትውልድም አዲስ የፖለቲካ ባህል ማስተላለፍ እንደምንችል ያረጋገጥንበት ነው በማለት፤ በውይይቱ ላይ ተሣታፊ የነበሩትን ፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በየዘርፉ የመወያያ መነሻ ሃሳብ ያቀረቡ ባለሞያዎች፣ ከተለያዩ ማኅበራት የተጋበዙ ታዛቢዎች፣ ውይይቱን ያስተባበረውን አጋር ድርጅት፣ በስምንቱ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተሣተፉ አወያዮች እንዲሁም ሂደቱን ሲያስተባብር የነበረው የቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳዮች ሥራ ክፍልን አመስግነዋል። በንግግራቸውም ማጠቃለያም ዋና ሰብሳቢዋ በስምንት የተመረጡ ሀገራዊ ጉዳዮችና ከ50 በላይ በሆኑ ንዑሳን ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተደረጉ ውይይቶች ላይ የተገኙትን ምክረ-ሃሳቦችን ያካተተው ሠነድ እንዲሁ ሼልፍ ላይ የሚቀመጥ ሣይሆን፤ በቀጣይ ለሚኖሩ ውይይቶችና ድርጊቶቻችን መስፈንጠሪያ ሊሆን እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል።
ቦርዱ በዐዋጅ እንደ አዲስ መቋቋሙን ተከትሎ ከተሠሩ በርካታ ሥራዎች ውስጥ፤ ከግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከአንድ ዓመት ለበለጠ ጊዜ በስምንት የተመረጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ፤ ማለትም የመድብለ ፓርቲ ግንባታ፣ ምርጫና ምርጫ ነክ ጉዳዮች፣ ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች፣ የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና የሕግ አስፈጻሚ አካላትን በተመለከተ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ መልካም አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ምሥረታና ተያያዥ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ራሳቸው እንዲያረቁት በተደረገ የውይይት ሥርዓት ማስጠበቂያ ደንብ አማካኝነት እንዲወያዩ በማድረግ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ጠቃሚ የሆኑ የወል ትርክቶች እንዲፈጠሩ የሚያስችል ውይይቶችን ማስተባበሩ ተጠቃሽ ነው።