ተስፋዬ ንዋይ
ተስፋዬ ንዋይ
አቶ ተስፋዬ ነዋይ በመንግሥት ሥራ (በሕዝብ አገልግሎት) ከ17 ዓመታት በላይ ማለትም በዐቃቤ ሕግነት፣ በሰብሳቢ ዳኝነት፣ በሕግ ጉዳዮች ተመራማሪነት እንዲሁም በዩንቨርስቲ መምህርነት አገልግለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንትና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል ዐቀባይ ሆነው አገልግለዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ የሁልጊዜ ደራሲ ሲሆኑ፤ እስካሁን በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ አምስት እንዲሁም በሥነ-አመራር ላይ የሚተኩሩ ሁለት መጻሕፍት ደራሲ ናቸው፡፡ በተጠቀሱት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከኻያ በላይ የምርምር ጹሑፎችን በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች በመጻፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡
እንደ ፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንትነታቸው ደረጃውን የጠበቀ የፍትሕ ሥርዓት እንዲሰፍን ብሎም ጥራት ያለው ፍትሐዊ እና ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት እንዲሰጥ እና የዳኝነት ነፃነትን ከተጠያቂነት ጋር ሚዛኑን አስጠብቆ እንዲሠራ፤ እንዲሁም በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች ለፍትሕ መጠናከር ተቀናጅተው እና በትብብር እንዲሠሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡
በአመራር ብስለት እና መሰል ስራዎቻቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ፤ አቶ ተስፋዬ በብሔራዊ ደረጃ በሙያቸው ለሀገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዜጎች የሚበረከተውን የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ከተሰጣቸው ሙያዊ ኃላፊነት ባሻገር በተለያዩ ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ላይ የነቃ ተሣትፎ የሚያደርጉ፤ የካበተ የሕይወት ልምድ ካላቸው የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ (መወያየት)፣ የተለያዩ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቦታዎችን የመጎብኘት ዝንባሌ አላቸው፡፡