ሐምሌ 12 2010   

መረጃ -1 

በተለያዩ አዋጆች ተካተው የሚገኙ ምርጫን ፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም የምርጫ ስነምግባርን የሚመለከቱ ህጎች ጠንካራ ጎናቸውን እንዳለ በመጠበቅ በህግ ማእቀፎቹ ውስጥ የተገኙ ክፍተቶችን ከመዝጋት፣ ግልጽነታቸውን ከማሳደግ እና አፈጻጸማቸው የተሳለጠ እንዲሆን ከማስቻል አንጻር አስፈላጊ ማሻሻያዎች ተደርጎባቸው በአዲሱ ህግ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ተካትተዋል።

ምርጫና አፈጻጸሙን በሚመለከቱት የረቂቁ ክፍሎች ውስጥ የተደረጉት ዋና ዋና ማሻሻያዎች የሚከተሉት ናቸው።
1) በህገ መንግስቱ አንቀጽ 61 (3 መሰረት በክልል ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት የሚደረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ምርጫ ከጠቅላላ ምርጫ ጋር እንዲካተት ማድረግ።
2) ክልሎች የአካባቢ ምርጫን በተመለከተ በውክልና የሚያወጧቸው ህጎች በህገ መንግስቱ እና በረቂቅ አዋጁ ከተቀመጡ ምርጫን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑና እንዳስፈላጊነቱ ለሁሉም አካባቢ ምርጫዎች የሚውሉ ተመሳሳይ መለኪያዎችን የሚያስቀምጥ ህግ እንዲወጣ ማስቻል።
3) ህዝበ ውሳኔን በማስፈጸም ረገድ ቦርዱ የሚኖረው ሚናና አፈጻጸምን የተመለከቱ ጉዳዮችን ማካተት።
4) የምርጫ ክልሎች የሚካለሉበትን እና ባወሳሰኑ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ክርክሮች የሚፈቱበትን አካሄድ በግልጽ ማስቀመጥ።
5) የምርጫ ጣቢያ እና የምርጫ ክልል ምርጫ አስፈጻሚ እና የአቤቱታ ሰሚ ኮሚቴዎች አባላት የሚሰየሙበትንና የሚመረጡበትን ሁኔታ ነጻነትን፣ ገለልተኛነትን፣ ብቃትን፣ አሳታፊነትን እና የጾታ እኩልነትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ማስቻል።
6) በአንድ የምርጫ ክልል ሊወዳደሩ የሚችሉ የእጩዎችን ቁጥር ገደብ እንዲሁም የፓርቲ እና የግል እጩዎች ሊካተቱ የሚችሉበትን ቅደም ተከተል የሚወሰንበት ሁኔታ ከአለም አቀፍ መርሆች እና ባገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ሆኖ በመገኘቱ እንዲቀሩ በማድረግ ሌሎች የእጩዎችን ቁጥር በጣም እንዳይበዛ ለማድረግ የሚያስችሉ መስፈርቶችን (ተጨማሪ የፊርማ ብዛትና ብር ማስያዝ)ማካተት።
7) ለወደፊት ቋሚ የመራጮች መዝገብ እንዲኖር እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለምርጫ መጠቀም የሚያስችል የህግ ማእቀፍ እንዲኖር መሰረት ማስቀመጥ።
8) በመራጭነት እና በእጩነት ለመመዝገብ መሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች በግልጽ በማስቀመጥ አንድ ሰው በምርጫ ክልሉ የኖረበትን ጊዜ የሚመለከተውን መስፈርት ማሳጠር።
9) ከቄያቸው በተለያየ ምክንያት ርቀው የሚገኙ ዜጎች፣ የአካል ጉዳተኞች እና ሌሎች የተለየ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በምርጫ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ የህግ ድንጋጌዎችን ማካተት ወይም ማስቻል።
10) የምዝገባን፣ የተቃውሞ አቤቱታና ውሳኔን፣ የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ግልጽ የሚሆንበትን፣ እጩዎች ሊተኩ የሚችሉበትን እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች የሚመለከቱ የጊዜ ገደቦች በግልጽና በቁርጥ እንዲቀመጡ ማድረግ።
11) በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን እና የመሳሰሉ ለምርጫ እንቅስቃሴ መዋል የሚችሉ ንብረቶችን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችል ስርዓት ማስቀመጥ።
12) የምርጫ ቅስቀሳ ሊካሄድ የሚችልባቸው ቦታዎች ላይ የተቀመጠውን ገደብ ምክንያታዊና ገዳቢ እንዳይሆን ማድረግ።
13) የድምጽ ቆጠራ ሂደት ግልጽ እና አስተማማኝ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ማስቻል፣ ቆጠራውን በተመለከተ የሚነሱ ቅሬታዎች አፋጣኝ ምላሽ የሚያገኙበትን አካሄድ መፍጠር እና የድም ቆጠራ ውጤት ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ እንዲገለጽ ማድረግ።